የምግባረ ሠናይ ሥራዎች
‘’ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ፥ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው።’’ ያዕ. 1፡17
አረጋውያን በዕድሜ ሳቢያ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለማቃለል ማህበራዊ ደህንነታቸውን ማረጋገጥ የጋራ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። በዓለማችን፣ በሀገራችን ብሎም በመዲናችን አዲስ አበባ በፈጣን ሁኔታ እያደገ የመጣው የአረጋውያን ብዛት በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ዘርፉ ቀውስ እንዳያስከትል ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። አረጋዊነት በሕዝብ ጤና ዘርፍ የሚመዘገብ ውጤት ነው፡፡ አረጋውያን ለኅብረተሰብ የሚጠቅም ዕውቀትና ችሎታቸውን በመጠቀም ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያደርጉ መርዳት ይጠበቅብናል።
በሰው ልጆች አኗኗር ውስጥ ያለው የመተሳሳብ የመረዳዳትና እና የመከባበር ባህል ከክርስቶስ የማያልቅ ፍቅር የመነጨ መሆኑ ለሁላቸችን ግልጽ ነው፡፡ ፍቅር ሁሉ ነገር ነውና ለደከሙት ብርታት፣ ለታመሙ ፈውስን፣ ተስፋ ላጡት ተስፋን ይሠጣል፡፡ ይሁንና ይህን ክርስቲያናዊ ፍቅር ማግኘት ከሚገባቸው ማህበረሰብ ወጥተው ጎዳና የወጡ፣ የሰው እጅ የሚጠብቁ በርካታ አረጋውያንን ማየት የተለመደ አጋጣሚ እየሆነ መጥቶአል፡፡
እነዚህ አረጋውያን እናቶችና አባቶች በህይወት ዘመናቸው የሚችሉትን ሁሉ አቅምና ጉልበታቸው ባልደከሙበት ወቅት በየተሰማሩበት የሥራ መስክና ሞያ ለሀገራቸውና ለወገናቸው የበኩላቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል። ዛሬ ግን አብዛኛዎቹ አረጋውያን ያለ ጠዋሪና ደጋፊ በየጎዳናውና ቤተ እምነቶች ደጃፍ ወድቀው ይገኛሉ።
በዚህ ሰብአዊ መብት እንዲከበር የሰው ልጆች ሁለንተናዊ ደህንነት እንዲጠበቅ እየተሰበከ ባለበት ዘመን በየአጥቢያ አብያተክርስቲያናት በር ተኮልኩልው ያሉ አረጋውያንን እና አረጋውያት ቁጥራቸው ብዙ ከመሆኑም ባሻገር መጠነ ሰፊ ችግር ላይ የወደቁ ናቸው፡፡ ከችግሩ ስፋት አኳያ ድርጅቱ “በእውነት ባልቴቶች የሆኑትን ባልቴቶች አክብር“ 1ኛ ጢሞ. 5፡3 ተብሎ እንደተጻፈ ክብረ አረጋውያን የማስጠበቅ ሥራ ይሠራል፡፡
