በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት የፈነጠቀው የልማት ጀምበር ለሁሉም መዳረስ እንደሚገባው ተጠቆመ
ግንቦት ፮ ቀን ፳፻፲ወ፰ዓ.ም.
ኢኦተቤክ_ቤሕአልድ
አዲስአበባ ኢትዮጵያ
በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የምስካየ ኅዙናን መድኀኔዓለም ገዳም የበላይ ኀላፊ የሚመራው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት ለስብከተ ወንጌል፣ ለልማት፣ለቴክኖሎጂና ለሚዲያ ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት አንቱታን ያተረፈ ሲሆን በ2018ዓ.ም በጀት ዓመት በርካታ የልማት ሥራዎችን አከናውኖ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በዛሬው እለት ገብኝተውታል።
በጉብኝቱ ቅዱስ ፓትርያሪኩን ጨምሮ ሁሉም የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትና የጽሕፈት ቤቱ ማኅበረሰብ የተገኙ ሲሆን በኮሪደርና የወንዝ ዳር ልማት ምትክ ከከተማ መስተዳድር የተሰጠውን በአራዳ ክፍለ ከተማ አራት ኪሎ አካባቢ የሚገነባውን ሕንጻ አበውንና ሌሎች ጅምር ሥራዎች ተካተዋል ።
ጉብኝቱ አዳዲስ ሥራዎችን ማዕከል ያደረገ ቢሆንም ከ9 ዓመታት በፊት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ዲዮርቆሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ በነበሩበት ዘመን ተጀምሮ ለዓመታት ሳይፈጸም የቆየውን በአሮጌው ቄራ አካባቢ የሚገኘው ባለ 10 ወለል ሕንጻ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ቆራጥ አመራር ሰጭነት ሥራው ተጠናቆ በቅዱስነታቸው ቡረኬ በዛሬው እለት ተመርቋል።
ከቅጥር ጊቢ ውጪ ከአራት ቦታዎች በላይ ጉብኝት የተደረገ ሲሆን በቅጥር ጊቢ ውስጥ የሚገነባውን ዘመናዊ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ፣ የከርሰ ምድር ውሃና ዙሪያ ገባውን የተሠራው ጊቢውን የማስዋብ ሥራ የጉብኝቱ አካል ነበር።
በመጨረሻም የቤተክርስቲያንን ክብርና ዝና የሚመጥንና ዘመኑን የዋጀ የአስተዳደር ስርዓት ለመዘርጋት እንዲያመች ተደርጎ የታደሰው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በተገኙበት የተመረቀ ሲሆን እድሳቱም ሆነ ልማቱ የቅዱስ ሲኖዶስ አባልትን እጅ በአፍ ያስጫነ ሆኗል።
በጉብኝቱ የተገኙ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና ሌሎችም ይህ የልማት መነሳሳት ለሌሎችም እንዲደረስ ጠንክሮ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን በመጠቆም በጉብኝቱ ስለተመለከቱት ሁሉ አድናቆቻቸውን ገልጸዋል።

