ታሪክ
መግቢያ
ጥንታዊት፣ታሪካዊትና ብሔራዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከምታስተዳድራቸውና ከምታንቀሳቅሳቸው ልማታዊ ተቋማት አንዱና ዋነኛው ከ1966ዓ.ም. በፊት የነበሩት ደጋግ የሀገሪቱ መሪዎችና የእምነቷ ተከታዮች በሕይወት በነበሩበት ወቅት በስጦታ፣ በሚያልፉበትም ጊዜ በኑዛዜ ለገዳማት መተዳደሪያ ያወረሷቸውን በቀጣይም በየጊዜው ራሷ ያስገነባቻቸውን ቤቶችና ሕንጻዎች በቤቶችና ሕንጻዎች የልማት ድርጅት አማካኝነት በእምነትና በጥንቃቄ ጠብቃና አስጠብቃ ከቤቶችና ሕንጻዎች በሚገኘው ገቢ ራሷንና ሀገርንም ሆነ ወገንን ጠቅማ መኖሯ ገሐድ ነው፡፡
ይህም በመሆኑ የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደር የልማት ድርጅት ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በየጊዜው የውስጥ አሠራሩንና አደረጃጀቱን በማሻሻል በተለይም ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ባደረገው ከፍተኛ የሥራ እንቅስቃሴና ባሳየው ታላቅ የለውጥ ሂደት ነባሮችን ቤቶችና ሕንጻዎችን በመጠገንና በማደስ ለኑሮና ለሥራ ምቹ አድርጎ በማከራየት የተከራዮችን ፍላጎት በማርካት ላይ ከመሆኑም ባሻገር አዳዲስና ዘመናዊ የሆኑ ሕንጻዎችን በማስገንባት የተከራዮችን ፍላጎት የበለጠ ለማርካትና የደንበኞችን ፍላጎት ለማሟላት ብሎም የቤተክርስቲኗን ገቢ ለማሳደግ በከፍተኛ ጥረትና እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡
የልማት ድርጅቱ ባለፉት ዓመታት ያገኘውን የሥራ ልምድ መሠረት በማድረግ ይበልጥ ጥረቱን አጎልብቶ በሂደት የታዩትን ድክመቶች በማረም በተከታዮቹ የበጀት ዓመታት ሥራዎችን ደንበኛ ተኮር፣ፍትሐዊነት፣ ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ቀልጣፋነት ያለውን አመራር ተከትሎ በመሥራትና ወቅታዊ የእርምት ርምጃ በመውሰድ የተገኘውን ውጤት ለማሳካት በሚያስችል መልከ የአለማቸው ሥራዎች ደረጃ በደረጃ እንዲከናወኑ በማድረግ ቤተክርቲያን የሰነቀችውን ራዕይ ተልእኮና ዓለማዎችን ለመተግበር እየሠራ ነው፡፡
የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት አመሠራርት
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ በሁሉም መስከ ባለጸጋ ናት ማለት ይቻላል፡፡ ሌላውን ትተን የመሬትንና የገንዘቡን ጉዳይ ብናይ ይህንኑ ያረጋግጥልናል፡፡ በጥንት ጊዜ የቤተ ክርስቲያን የሀብት ምንጭ በዓሥራት በኵራት አማካኝነት የሚገኝ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ነገሥታቱና መኳንንቱ ከነበራቸው ሀብትና ንብረት ቀንሰው ለቤተ ክርስቲያን ከሚሰጡት (ከሚያወርሱት) ሌላ በስጦታ የሚያገኟቸውን ውድ ዕቃዎችና የከበሩ ማዕድናትን ለቤተ ክርስቲያን ነበር የሚያስረክቡት፡፡ ከዐፄ ይኵኖ አምላክ ጊዜ ጀምሮ ግን ቤተ ክርስቲያን የሢሦ መሬት ባለቤት ጭምር ሆነች፡፡ ይሁን እንጂ የቤተ ክርስቲያን መሬት፡-
1. መንቀያና መትከያ የአገልግሎት ርስት 2. ሁዳድ 3. ሪም ወይም ቀላድ 4. የመስቀል መሬት
በሚል ሥርዓት፣ ሕግና ደንብ ወጥቶለት ሥራ ላይ የዋለው ከመጋቢት 1 ቀን 1934 ዓ.ም ጀምሮ ነበር፡፡ከላይ በተጠቀሰው ደንብ መሠረት ቤተ ክርስቲያን ሕጋዊ ርስት እንዲኖራት ከመደረጉ ባሻገር ከርስትዋ ግብር የመሰብሰብ መብትም ተሰጥቷት ነበር፡፡ በመሆኑም ደርግ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕንጻዎች ድንገት ከመውረሱ በፊት ቤተ ክርስቲያናችን ከሕንጻዎች ኪራይ፣ ከመሬት ግብርና ከርስተ ጉልት ገቢ በዓመት ከሠላሳ ሦስት ሚሊዮን ሰባት መቶ ሺሕ ብር በላይ ገቢ ታገኝ ነበር፡፡ ይሁንና ደርግ በቅድሚያ በየካቲት ወር 1967 ዓ.ም ‹‹መሬት ላራሹ›› በሚል ባወጣው ዓዋጅ በምዕረብ ሸዋ ዞን (አምቦ) አካባቢ ተቋቁመው የነበሩ የጉደር የወይን እርሻና የወይን ጠጅ ፋብሪካ፣ በመናገሻ አካባቢ የነበረው ዘመናዊ የእርሻ ጣቢያ፣ በምዕራብ ትግራይ በብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ጥረት ለኵናማ ማኅበረሰብ አገልግሎት እንዲሰጡ ተቋቁመው የነበሩ ሰፋፊ የልማት አውታሮች፣ በከፋ ለቅዱስ ጳውሎስ ት/ቤት ገቢ ማስገኛ ተብሎ ተከፍቶ የነበረው ሰፊ የቡና ተክል እርሻ ወዘተ… ወረሰ፡፡
ደርግ በዚህ እርምጃው ሳያበቃ በየክፍለ ሀገሩ የነበሩ የልማት ቦታ ዎችን፣ የእርሻና የመስኖ ስፍራዎችን በመውረስ የሀገሪቱ የሃይማኖት፣ የቅርስና የታሪክ ማእከላት የነበሩትን ገዳማትና አድባራት ያለገቢ አስቀራቸው:: በመቀጠልም በሐምሌ ወር 1967 ዓ.ም የከተማ ትርፍ ቤቶች ዓዋጅ በሚል አዲስ አበባን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ የነበሩና በነገሥታት፣ በመኳንንትና ግለሰቦች በውርስና በስጦታ ለቤተ ክርስቲያንዋና ለተለያዩ ገዳማት የተሰጡና ቤተ ክርስቲያንዋ በማእከል ደረጃ በራሷ ገንዘብ የገነባቻቸውን ሕንጻዎች ወረሳቸው:: እንደ እውነቱ ከሆነ ከላይ የተጠቀሱት የቤተክርስቲያንዋ ሀብቶች ‹‹ትርፍ›› ሳይሆኑ ቤተ ክርስቲያንዋ የምትተዳደርባቸው ቋሚ በጀት ማስገኛ ተቋማት ነበሩ፡፡ ከሁሉ የሚያስገርመው ደርግ በከተሞች የነበሩትን ሕንጻዎችና ተቋማት ኢ-ሕጋዊ በሆነ መንገድ መውረሱ ሳያንስ በጠቅላይ ቤተ ክህነት መንበረ ፓትርያርክ ጽ/ቤት ቅጽር ግቢ የነበሩትን የቅዱስ ፓትርያርኩ ማዕድ ቤት፣ የእንጀራና የወጥ ቤት፣ የጠላና ጠጅ ቤት፣ የእህል ጐተራ፣ ዕቃ ቤት፣ የእንግዶና የመኮሳት መኖሪያ የነበሩት ሁሉ የመውረሱ ጉዳይ ነበር፡፡
በዚህ የተነሣ በወቅቱ የነበሩት ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የዕለት ተዕለት ሥራቸውን ለማከናወን በእጅጉ ተቸግረው እንደነበር የጠቅላይ ቤተ ክህነት ተጠባባቂ ሥራ አስኪያጅ የነበሩ መርስዔ ኀዘን አበበ ሐምሌ 12 ቀን 1972 ዓ.ም በቁጥር 6242/22/72 ለኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ለከተማ ልማትና ቤት ሚኒስትር ከጻፉት የአቤቱታ ደብዳቤ መረዳት ይቻላል፡፡ በተመሳሳይ የቆዩ የመዝገብ ቤት ሰነዶችን ፈትሸን ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ደርግ የመንበረ ፓትርያርክ ቅጽር ጊቢ ቅዱስ ፓትርያርኩ ጓዳ ድረስ በመገባት የወረሳቸውን ማዕድ ቤትና ዕቃ ቤት ለ16 ሰዎች ፣ የእንግዶች ማረፊያውና የመነኮሳት መኖሪያዎችን ለሌሎች 10 ሰዎች ነበር ያደለው፡፡
በዚህ የተነሣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት መንበረ ፓትርያርክ ጽ/ቤት መሥሪያ ቤትንና መኖሪያ ቤትን በአንድነት አጣምሮ እንዲይዝ በመገደዱ ነዋሪዎችንና ባለጉዳዮችን፣ ነዋሪዎችንና ሠራተኞችን ለመለየት ከማይቻልበት ሁኔታም ተደርሶ ነበር፡፡ ይህ ዓይነቱ ትርምስ ባስከተለው ችግርም የግቢውን ጸጥታ በአግባቡ ለመምራትም ሆነ የቅዱስ ፓትርያርኩን ዕለታዊ ተግባር በአግባቡ ማከናወን አዳጋች የሆነበት ጊዜም ነበር፡፡
በደርግ ተወርሰው የነበሩ የቤተ ክርስቲያንዋ ሕንጻዎችና ቤቶች የአመላለስ ሂደት
5ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የቤተ ክርስቲያኒቱን ርእሰ መንበርነት ከተረከቡ በኋላ ካከናወኑዋቸው ዐበይት ተግባራት መካከል በደርግ መንግሥት በግፍ ተወርሰው የነበሩትን የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕንጻዎች፣ የትምህርት እና የእደ ጥበባት ተቋማት እንደዚሁም የተለያዩ ድርጅቶችን የማስመለሱ ሂደት ነበር፡፡ እነዚህን ተቋማት ለቤተ ክርስቲያኒቱ እንዲመልስ በወቅቱ ለነበረው የሽግግር መንግሥት ጥያቄ ከመቅረቡ በፊት የተወረሱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቋሚ ሀብቶች (ሕንጻዎች፣ ቤቶች፣ ፋብሪካዎች ወዘተ) የትና በምን ሁኔታ እንደሚገኙ ቊጥራቸውንና ይዘታቸውን የሚገልጽ ማስረጃ የማሰባሰቡ ሂደት ነበር የተከናወነው፡፡ ይህንን ሁኔታ የሚከታተሉና የሚያስፈጽሙ ኮሚቴዎችም በጠቅላይ ቤተ ክህነትና በአህጉረ ስብከት ደረጃ እንዲቋቋሙ ተደርገው ነበር፡፡
በዚህ አድካሚና እልህ አስጨራሽ በነበረው መረጃን የማሰባሰብ ሂደት አቶ ታደለ ገብረ መስቀልና መምሬ ተዘራ ወርቁ የማይተካ ሚና ነበራቸው:: መረጃዎች ከየቦታው ከተሰባሰቡ በኋላ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በደርግ የተወረሰ-ቤቶችና ተቋማት ለቤተ ክርስቲያንዋ እንዲመለሱ የካቲት 17 ቀን 1986 ዓ.ም በቊጥር 2923/22/86 በተጻፈ ደብዳቤ ጠየቁ፡፡ ይህ በቅዱስነታቸው የተጻፈው ደብዳቤ በዋናነት በአራት ኪሎ መንበረ ፓትርያርክ ዙርያ ያለው ቦታና ቤቶች እንዲመለሱ የሚጠይቅ ነበር፡፡ በሌላ በኩል በዋና ጸሐፊው በአቶ ገዛኸኝ ያይንሸት በ3/6/87 በቁጥር 2823/2287 ዓ.ም ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የተላከ ሌላ ደብዳቤ እንዲመለሱ የተጠየቁት የ119 ሕንጻዎችና ቤቶች ዓይነትና ብዛት ዝርዝር የያዘ ነበር፡፡ ይህንን የቤተ ክርስቲያንዋን ጥያቄ በቀናነት የተመለከቱት የቀድሞ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ የካቲት 6 ቀን 1987 ዓ.ም በቁጥር 0030-አጠ1/01/02 በተጻፈ ደብዳቤ በደርግ ተወርሰው የነበሩ ሕንጻዎችና ቤቶች ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን እንዲመለሱ የሚያበሥረውን ደብዳቤ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት እንዲደርስ አደረጉ፡፡
ይህች ዕለት ለቤተ ክርስቲያን “ልዩ የደስታ ቀን›› ነበረች ማለት ይቻላል፡፡ ቤቶችን ለማስመለስ በተደረገው ጥረት ከቅዱስ ፓትርያርኩ ቀጥሎ ብፁዕ አቡነ ገሪማ፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት አቶ ገዛኸኝ ያይንሸት (በወቅቱ የጠቅላይቤተ ክህነት ዋና ጸሐፊ) አቶ ትኳቦ በርሄ፣ አቶ ታደለ ገብረ መስቀል፣ መምሬ ተዘራ ወርቁ፣ አቶ ዮሐንስ ገብረ ሥላሴ፣ ቄስ በላይ ተገኝ፣ አቶ አበራ ሀብቴ፣ አቶ ኤልያስ ሞላ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው፡፡
የኢፌድሪ መንግሥት በደርግ ተወርሰው የነበሩ የቤተክርስቲያንዋን ሕንጻዎችና ቤቶች መመለስ በጀመረበት ወቅት ቤተ ክርስቲያን የምትረከባቸውን ቤቶች ለማስተዳደር የሚያስችላት መዋቅር፣ የሰው ኃይልና የገንዘብ አቅም አልነበራትም፡፡ በመሆኑም በወቅቱ ይህን ጊዚያዊ ችግር ለመፍታት የተወሰደው እርምጃ የተረከበቻቸውን ቤቶች አጫርታ ዘመናዊ የቤቶች አስተዳደር ሞያ ላለው ድርጅት (Real Estate Management) ለአንድ ዓመት በኮንትራት መስጠት የሚል ነበር፡፡
በዚህ መሠረት ይህንን የሚያስፈጽም በብፁዕ አቡነ ገሪማ የሚመራ፣ በአባልነት
- አቶ ጥላሁን ወርቅ
- አቶ ገብረ ሚካኤል ወርቅነህ
- አቶ ቆስጠንጢኖስ በርሔ
- ኢንጂነር ገብረመስቀል ተስፋየ
- አቶ ገብረ እግዚአብሔር
- አቶ ትኳቦ በርሄ
ያካተተ ኮሚቴ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ትእዛዝ በ1/5/88 በቊጥር 63/187/88 በተጻፈ ደብዳቤ ተቋቋመ፡፡
ኮሚቴው ባወጣው ጨረታም 27 ተወዳዳሪ ድርጅቶች ቀርበዋል፡፡ በመጨረሻም ሥዩምና አምባዬ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ አሸናፊ ሆኖ ተመረጠ፡፡ በማከታተልም በአቶ ትኳቦ በርሄ ሰብሳቢነት 1. መምሬ ተዘራ 2. አቶ ታደለ ገብረ መስቀል 3. አቶ አበራ ሀብቴ 4. ቄስ በላይ ተገኝ ያካተተ የጊዜያዊና የቋሚ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ቤት ተቋቋመ:: የዚህም ጽ/ቤት ኀላፊነት ቤተ ከርስቲያንዋ በተረከበቻቸው ሕንጻዎች መካከል የሚገኙ ክፍት ቦታዎችን በጥናት በመለየት ማቅረብና በመሐንዲስ የቀረቡትን ቦታዎችን እያጠና አዳዲስ ሕንጻዎችን እንዲሠራ ማድረግ የሚል ነበር፡፡ሥዩምና አምባዬ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ ከየካቲት 1 ቀን 1989 ዓ.ም. ቤቶችን የማስተዳደር ሕጋዊ ውክልና ተቀብሎ ቤቶችንና ሕንጻዎችን ማስተዳደር ማለትም ማከራየት፣ ማደስ ወዘተ ጀመረ፡፡ ድርጅቱ ሥራውን በጀመረበት ወቅት ተረክቦ የስተዳድራቸው የነበሩ ሕንጻዎች
- ቤተ ዮርዳኖስ
- ጽርሐ ምኒሊክ
- ዘውዲቱ
- የቤተክህነት ሕንጻዎች ( በቁጥር ሦስት)
- ሐረር ሀገረ ስብከት
- ሽረጋ ሕንጻ ነበሩ በዚህ ወቅት ከእነዚህ ሕንጻዎች የወር ገቢ ብር 30983 .20 ሲሆን የተከራዮቹ ብዛት 153 ብቻ ነበሩ፡፡
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር መለስ ዜናዊ በመንግሥት እጅ የነበሩ ቤቶችና ሕንጻዎች ለቤተ ክርስቲያንዋ እንዲመለሱ ለሚመለከታቸው አካላት በደብዳቤ ቢያዙም የማስመለሱ ሂደት ቀላል አልነበረም፡፡ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፊርማ በቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተላኩ ከሁለት በላይ የአቤቱታ ደብዳቤዎችና በዋናው ሥራ አስኪያጅ በብፁዕ አቡነ ገሪማና በዋና ጸሐፊው አቶ ገዛኸኝ ያይንሸት አማካኝነት የርክክቡ ሥራ መጓተቱን በተመለከተ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት፣ ለመንግሥት ኪራይ ቤቶች : ለአዲስ አበባ መስተዳደር የተጻፉ ተደጋጋሚ ደብዳቤዎች ለዚህ ማሳያ ናቸው::
ከጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ከኪራይ ቤቶች አስተዳደርና ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የተውጣጡ የኮሚቴ አባላት ተመድበው ሥራውን ለማቀላጠፍ ቢሞከርም ቢሮክራሲያዊው አሠራር ሂደቶች በታሰበው መልክ እንዳይጓዙ እንቅፋት መፍጠሩ አልቀረም:: በዚህ አጋጣሚ ከቤተክህነት ተወክለው ይሠሩ ከነበሩት በተጨማሪ ከኪራይ ቤቶች አስተዳደር 1. አቶ ደረጀ መንገሻ 2. አቶ ግርማ ገብረ ሥላሴ 3. አቶ ታፈሰ ደሜ 4. አቶ አረጋ ውባለ 5. ወ/ት ሰላማዊት ዮሴፍ (በአስረካቢነት) ተመድበው ሠርተዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጽ/ቤት ወክለው በቤቶች ማስመለስ ሂደት በኃላፊነት ሲሠሩ የነበሩት በወቅቱ በኢትዮጵያ ሽግግር መንግሥት የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽ/ቤት የማኅበራት ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ አቶ እንዳልካቸው መርዕድ ነበሩ፡፡
ሥዩምና አምባዬ ለአንድ ዓመት ያህል ቤቶችና ሕንጻዎችን በውክልና (ኮሚሽን) ሲሠራ ከቆየ በኋላ «የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የንብረት፣ የኢንቨስትመንት የአስተዳደር የልማት ቦርድ›› የሚል ሥያሜ የተሰጠው ጥር 15 ቀን 1990 ዓ.ም ተቋቁሞ ተረክቦታል፡፡ የዚህ ቦርድ የመጀመሪያ የቦርድ አባላት
- ብፁዕ አቡነ ገሪማ ሰብሳቢ
- አቶ ዓለማየሁ ኀይሌ አባል
- ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ አባል
- ዶ/ር መኮንን መሸሻ አባል
- አቶ አሥራት በቀለ አባል
- አቶ ቴዎድሮስ ወንዲራድ አባል ነበሩ፡፡
ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደተሞከረው በመኳንንት፣ በወይዛይርትና በግለሰቦች አማካኝነት በውርስ፣ በኑዛዜና በስጦታ መልክ ለቤተ ክርስቲያን ከተሰጡ ሕንጻዎች መካከል ሠላሳ ሰባቱ (37) በገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት ስም የተመዘገቡ ነበሩ፡፡ ዋና ዋና ናዎቹ የቤተክርስቲያንዋ ሕንጻዎች በማን እንደተበረከቱና እንደተሠሩ ለማወቅ የሚከተለውን ሰንጠረዥ ማየት ይቻላል፡፡
| ተ.ቁ | የሕንጻው ስም | ሕንጻውን ለቤተክርሰቲያን የሰጠው ሰው ወይም ድርጅት |
| 1 | ዘውዲቱ | የታዕካ ነገሥት በዓታ ገዳም ባለ አደራ ቦርድ ያሠራው |
| 2 | ደብረ ጽጌ | ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ |
| 3 | መንበረ መንግሥት | የጊቢ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን |
| 4 | ሐረር ሀገረ ስብከት | የሐረር ሀገረ ሰብከት ቤተክህነት |
| 5 | ቤተ ዮርዳኖስ | ግርማዊት እቴጌ መነን |
| 6 | ጽርሐ ምኒሊክ | በበዓታ ሊቀ ሊቃውንት ጌታሁን (ኋላ አቡነ ሉቃስ) የተሠራ |
| 7 | ባንኮ ዲሮማ | ለምስካየ ኅዙናን ገዳም አጼ ሐ/ሥላሴ ያሠሩት |
| 8 | አፋር (ቁልቢ) | የሐረር ሀገረ ስብከት ቤተክህነት |
| 9 | ልማት ሕንጻ | ቤተክህነት በብላታ ልሳኑ ጊዜ |
| 10 | ጠጠር ሕንፃ | ቤተክህነት በብላታ ልሳኑ ጊዜ |
| 11 | አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የነበረው | ቤተክህነት በአቡነ ባስልዮስ ዘመን |
| 12 | ሸረጋ | ቤተክህነት በአቡነ ባስልዮስ ዘመን |
| 13 | ቴዎፍሎስ | ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ |
| 14 | አሰቦት | አፄ ሐ/ሥላሴ ለአሰቦት ገዳም የሰጡት |
| 15 | ኮምቦልቻ | አፄ ሐ/ሥላሴ ለአሰቦት ገዳም የሰጡት |
| 16 | ጉለሌ ክፍለ ከተማ | አቡነ ጴጥሮስ (የጎንደሩ) ያሠሩት |
| 17 | ልደታ ደብረ ጽጌ | ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ |
| 18 | ኢትሆፍ መጋዘን | ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ |
| 19 | ፍል ውሃ ፊንፊኔ (ዱከ) ሆቴል | አጼ ሐ/ሥላሴ ኪራዩ ለቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እድሳት እንዲሆን የሰጡት |
| 20 | ሲቪል ሰርቪስ | ቤተክህነት በብላታ ልሳኑ ጊዜ |
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደር ልማት ድርጅትን የመሩ ዋና ሥራ አስኪጆች ስም ዝርዝር
| ተ.ቁ. | ሙሉ ሥም | የመሩበት ጊዜ |
| 1 | አቶ አባይ ታደሰ | ከመጋቢት 11ቀን 1990 እስከ ታህሳስ 13 ቀን 1997 |
| 2 | መጋቤ ካህናት ኀ/ሥላሴ ዘማርም | ከታህሳስ 13 ቀን 1997 እስከ የካቲት 1 ቀን 1998 |
| 3 | ወይዘሮ አበባ ያዘው | ከየካቲት 1 ቀን 1998 እስከ የካቲት 20 ቀን 1999 |
| 4 | ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ | ከየካቲት 9 ቀን 1999 እስከ ጥር 15 ቀን 2000 |
| 5 | አቶ ተስፋዬ ጣፋ | ከጥር 15 ቀን 2000 እስከ የካቲት 21 ቀን 2003 |
| 6 | አቶ ተስፋየ ውብሸት | ከጥር 3 ቀን 2003 እስከ ጥቅምት 23 ቀን 20005 |
| 7 | መ/ብ ፍስሐ ጌታነህ | ከጥቅምት 23 ቀን 20005 እስከ ሰኔ 13 ቀን 2005 |
| 8 | አቶ ተስፋየ ውብሸት | ከሰኔ 13 ቀን 2005 እስከ ህዳር 23 ቀን 2009 |
| 8 | ሊ/ት ሽመልስ ቸርነት | ከጥቅምት 16 ቀን 2009 እስከ ግንቦት 11 ቀን 2012 |
| 9 | አ/መ አባ ገ/ሥላሴ ጌትነት | ከግንቦት 11 ቀን 2012 እስከ መስከረም 5 ቀን 2014 |
| 10 | መ/መዊዕ ሳሙኤል እሸቱ | ከመስከረም 5 ቀን 2014 እስከ ግንቦት 8 ቀን 2015 |
| 11 | ሊ/ት ሽመልስ ቸርነት | ከሰኔ 6 ቀን 2015 እስከ ነሐሴ 1 ቀን 2017 |
| 12 | ሊ/ሥ እስክንድር ገብረ ክርስቶስ | ከነሐሴ 1 ቀን 2017 |
